Saturday, April 30, 2016

“እንደ ተናገረ ተነሥቶአል”የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ቅዳሜ ሚያዝያ 22/2008 .
እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
 በመንፈሳዊ ዓለም ትልቅ ትርጉም ካላቸው ቃላት አንዱ ትንሣኤ የሚለው ቃል ነው። ትንሣኤ ከፊቱ ሞት አለ። ትንሣኤንም ተናፋቂ የሚያደርገው የሞት ገዥነት ነው። ሞት ነፍስን ከሥጋ ብቻ ሳይሆን ወዳጅን ከወዳጅ የሚለይ ነው። ሞት ሰው ሊዘለው የማይችል ትልቅ እንቅፋት፥ ከመንገድ የሚያስቀር መሰናክል ነው። ሞት የመልካምም የክፉ ሥራም ማብቂያ ነው። ሞት የሀዘን የስብራት መገኛ ነው። ይህን የሚቆርጥ ስለት፥ የሚያለያይ ግንብ፥ መልክ አፍራሽ ጨካኝ፥ እንባን የተጠማ ደግሞም የማይረካ ዳኛ የምንለያየው በትንሣኤ ብቻ ነው። ሞትን ገስጾ ትንሣኤን የሚያውጅ ለዘመናት አልተገኘም። ታላላቅ ግዛቶችን የገዙ ሞትን ግን ማሸነፍ አቅቶአቸው፥ የሁሉም መጨረሻ ሞተ የሚል ሆነ። ጠቢባን ሐኪሞች ሁሉ እስከ ሞት ድረስ ይሯሯጣሉ፥ ጠቢብም ይባላሉ። ሞት ሲመጣ ግን ከመቀመጥ ውጭ ቀጣይ ጥበብን ለማሳየት እንኳ አይግደረደሩም። ሞት ሕሊናን ጭምር የገዛ ነው። ሳይመጣ በስጋት፥ መጥቶ በሀዘን የሚጎዳ መርዝ ነው። ይህንን እናትና ልጅን የሚለየውን፥ ንጉሥን ከዙፋን አውርዶ አፈር ውስጥ የሚያስተኛውን፥ ያማረውን ገላ የሚያፈርሰውን፥ ስምን በደቂቃ ሰርዞ ሬሳ የሚያስብለውን፥ የሚሳሳውንና ቤቱን የማያምነውን ሰው ጨካኝ አድርጎ የማይመለስበትን መንገድ የሚያስጀምረውን ሞት ማን ድል እነሣዋለው ብሎ ይግደረደራል? ባለ አንድ መንገድ የሆነውን፥ መሄጃ እንጂ መመለሻ የሌለውን ይህን መንገድ ማን አስፍቶ ባለሁለት ጎዳና ያደርገዋል?
 ሞት፥ ሞት አጥቶ እስከ መቼ ይንጎማለላል? ሁሉን ውጦ እስከ መቼ ዝም ይላል? ዘመናትና አዝማናትን እያስረጀ ለምን ያስረሳል? ሞት በየትኛው ችሎት ይከሰሳል? በቃህ ተብሎ ገዥነቱን ማን ይነጥቀዋል? አዎ ገዥ ነውና ገዥ፥ በገዥ ይሻራል። ገዥን በፍላጎት ማሸነፍ አይቻልም። በሥልጣንና በኃይል የሚሽረው ያስፈልጋል። ይህን ሥልጣንና ኃይል የሚያሟላ ከፀሐይ በታች አልተገኘም። ሥልጣኑ ግዛትን የሚነጥቅ፥ ኃይሉ ያሰራቸውን ሰብሮ የሚያወጣ ነው። የሰው ልጅ በኃጢአት ምክንያት በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ፥ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ሲኦል ተፈርዶበት ሳለ፥ ሞትን በሞት የሚነቅል ታዳጊ መጣለት። እርሱም የትንሣኤው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ትንሣኤ ማለት መነሣት፥ መንቃት፥ እንደገና ለመኖር አቅምና ሥልጣን ማግኘት ነው። አንድ ሰው ለመኖር አቅም ያስፈልገዋል፥ እርሱም እስትንፋስ ነው። ሥልጣን ያስፈልገዋል። እርሱም ንጉሣዊ ፈቃድ ነው። ትንሣኤ በውስጡ መለኮታዊ ሥልጣን ያለው ነው። ከእግዚአብሔር በቀር እስትንፋስን የሚቀጥል፥ የመኖርን ፈቃድ የሚሰጥ የለምና። ሰው ገንዘብ እያለው ይሞታል፥ የነገሥታት ፈቃድ እያለውም ያሸልባል። ስለዚህ ሰማያዊ ሥልጣን ብቻ ትንሣኤን ያበስራል። ይህም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተገኝቷል። ትንሣኤን ከአሁን ህልውና ተነሥተን ስናስበው ያንስብናል። ከሞቱት ወገኖቻችን አንጻር ብናስበው ትንሽ ጎላ ይልልናል። እንደገና መጥተው ብናገኛቸው እንደገና ላንጣላቸውና ላንጠላቸው ቃል እንገባለን። የፈራነውና በደቂቃ ውስጥ ሞት ሲመጣ የሸሸነው ማንነታቸውን እንደገና እናቅፈዋለን። የሻርነውን ስማቸውን መልስን እንቀጽልላቸዋለን። ትንሣኤ ይቅርታንና ጠላትንነትን ያጠፋል። የተጸየፍናቸውን እንድንቀርብ ያደርገናል። ስማቸውን ያጠፋናቸውን በስማቸው እንድንጠራቸው ያደርገናል። ሞት ለከበባት ዓለም ትንሣኤ መልስ ነው። ዛሬም ትንሣኤ ብቻ የሚመልሰው ብዙ ሞት፥ ሞት የሚሸት ነገር አለ። በአገር፥ በትዳር በወዳጅነት መካከል ያለውን ችግር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ሽኩቻ ስናይ አልሞትንም ብለን መዋሸት ይቸግረናል። መልሱ ትንሣኤ ነው። በራስ ኃይል መቃብርን መጣስ፥ በራስም ሥልጣን ከመቃብር በላይ መጓደድ አይቻልም። የትንሣኤው ጌታ ያስፈልገናል።